የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

የኢትዮጵያ ውሹ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።
ጁኒየር ግራንድ ማስተር አቡበከር አህመድ የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት በጠቅላላ ጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት:- የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን አሰራርንና ደንብን በመከተል የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። ኢትዮጵያ በዘረፉ እንደ አፍሪካ ብዙ ስፖርተኛ ያላት ሀገር በመሆኗ ሀገራችን በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስክ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማስገኘት መንግስት በዘረጋው ደንብና የአሰራር ስርዓት በመከተል ለተሻለ ስራ መነሳሳት ያስፈልጋል ብለዋል።
አክለውም በስፖርተኞች እና በስፖርቱ ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም፣ የስፖርተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅና ስፖርተኞችም ግዴታቸውን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የጠቅላላ ጉባኤው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
አቶ ዳንኤል ደኜ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ማህበራት ምዝገባ፣ ድጋፍና ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ በበኩላቸው ማንኛዎ ስፖርት ፌዴሬሽን ዘርፉን ለማሳደግ እና ከመንግስት በጀት ለማግኘት ህዝባዊ አደረጃጀቱን እስከ ታችኛው መዋቅር ማውረድ አለበት። የስፖርቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ለማፈላለግ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው የ2016ዓ.ም የኦዲት ሪፖርት እና የዕቅድ ክንውን ሪፖርት፣ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ፣ የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ፤ የስነምግባር መመሪያ፤ የደረጃ እድገት መሰላል ሰነድ፤ የፋይናንስ መመሪያ የብቃት መመዘኛ ሰነዶች በአጀንዳነት ቀርቦ ውይይት ተደረጓል።
የፌዴሬሽኑ የገቢ እና የወጪ አወጣጥ ስርዓቱ ጤናማ መሆኑ፤ የገንዘብ አያያዝ በቃለ ጉባኤ እና በህጋዊ ሰነዶች የተደገፈ መሆኑ፤ ከሠራተኞች የሚቆረጠው የመንግስት ግብር ሳይሸራረፍ በሰነድ የተደገፈ ክፊያ መፈፀሙ፤ ፌዴሬሽኑ የራሱን ዕቅድ ማሳኪያ የሚሆን የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግ ረገድ ጥሩ ስራዎች መሰራቱ፤ ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ማስመረጥ መቻሉ፤ በስፖርት ዲፕሎማሲው እና ከአጋር አካለት ጋር በቅንጅት የተሰሩት ስራዎች አመርቂ ናቸው ተብሏል።
በአጠቃለይ የፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ መልካም የሆነ መሻሻል ውስጥ መሆኑ በጥንካሬ የተነሱ ጉዳዮች ሲሆኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አወቃቀሩ ክልሎችን ያማከለ አለመሆን፤ ውድድሮችን የማካሄዱ ተግባር ክልሎች እንዲያዘጋጁና ስፖርቱ በክልሎች እንዲነቃቃ አለመደረጉ፤ የስፖርቱን ኢንዱስትሪ ከማስፋፋት አኳያ የሚጠበቀውን ያህል አለመሰራቱ፤ ፌዴሬሽኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑ በውስንነት ተነስቷል።
ጉባኤው በቀረቡት መመሪያዎች ላይ መጨመርና መቀነስ የሚገባቸውን ሃሳቦችን በማዋጣት በዕለቱ የቀረቡትን አጀንዳዎች መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፀድቋል።
Scroll to Top